ስለእኛ
መጠሪያችን
በኢትዮጵያ የብልጽግና ሪፎርም የለውጥ ስራዎች በተለያዩ ተቋማት የነበሩ ስራዎችን በማሰተሳሰር እንደ አዲስ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡ በዚህም የኢፌዲሪ የኢምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በመባል ይጠራል፡፡
ታሪክ ምን ይላል ?
በወሳኝ ኩነት ምዝገባ፡- ከአጼ ሚኒሊክ ለውጭ ሀገር ዜጎች የልደትና የሞት ማስረጃዎችን በመስጠት አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረ የታሪክ ድርሳናት የሚያሳዩ ሰነዶች ያሉ ሲሆን ህጋዊ አሰራር ተከትሎ እንዲሰራ ለማድረግ የተጀመረው ግን በ1934 ዓ.ም ስለ ሀገር አገዛዝ የወጣውን የመንግስት ድንጋጌ መሠረት በሰባ አራተኛው ክፍል ከንቲባዎች ከሚፈፅሟቸው ሥራዎች አንዱ በሚል ርዕስ ሥር በፊደል ተራ ቁጥር “መ” ላይ የከተማውን ሕዝብ በክብር መዝገብ መፃፍ ማለት /ልደት፣ ጋብቻና ሞት/ መሆኑን ይገልፃል፡፡
ሌላው ስለሚኒስቴሮች ሥልጣን በተመለከተ በትዕዛዝ ቁጥር1/1935 ዓ.ም በቁጥር 36 በፊደል ተራ ቁጥር “መ” ለሀገር ግዛት ሚኒስቴር በተሰጠው የሕዝብ ቆጠራ፣ የጋብቻና የልደት የክብር መዝገብ ስለመጻፍ ሥልጣን በህጉ የተሰጠው ሲሆን ለማዘጋጃ ቤቶችም ውክልና በመስጠት  የሀገሪቱ ሕጎች በከተማው ክልል ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ለማስፈፀምና በሥራ ላይ ለማዋል አስፈላጊ የሆኑትን የውስጥ ደንቦች ለማውጣት የሚያስችል መብት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ በ1943 ዓ.ም በወጣው የሕግ ማስታወቂያ ቁጥር 15ዐ/43 መሠረት ለመቃብር የሚሆነውን ቦታ መወሰን፣ መቃብር መቆጣጠርና መዝግቦ መያዝ የሚሉት ለማዘጋጃ ቤት ከተሰጡ ተግባራት ተግባራት አንዱ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በ1952 ዓ.ም የወጣው የፍትሕ-ሐብሔር ህግ ውስጥም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ለመዘርጋት ተብለው በርካታ አንቀጾች እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ህግ በቁጥር3361(1) ህግ የክብር መዝገብ የሚመለከቱት አንቀጾች  ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የተለየ ደንብ እስከሚወጣ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዓላማው፣ ሂደቱና አፈፃፀሙ ከዘመናዊውና አግባባዊው ምዝገባ አሠራር አንፃር የመነሻ መሰረት የሚሆኑ ነጥቦች እንዲካተቱ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ያሉ ክፍተቶች እንዳሉ ሆነው  በተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች ማለትም ማዘጋጃ ቤቶች፣ የከተማ አስተዳደር ጽ/ ቤቶች፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ እና የጤና ተቋማት ወሳኝ ኩነቶችን የተመለከቱ ምዝገባዎች የማካሄድና መረጃዎችን የመሰብሰብ ስራዎች እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በዚህ በኩል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ በሀይማኖት ተቋማት ቀደም አይማኖታዊ አሰራሮቻቸውን ተከትለው ክስተቶችን የሚመዘግቡበት ስርዓት በሀገራችን በሂደቱ ሳይጠቀስ የማያልፍ ጉዳይ ነው፡፡
ስለዚህ በ1935 ዓ.ም የጋብቻ፣ በ1946 ዓ.ም የልደት፣ በ1962 ዓ.ም የሞት ምዝገባ ጀመረ፡፡ እነዚህም ምዝገባዎች የሚካሄዱት ለሕጋዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሚውሉ ማስረጃዎችን ለማግኘት በፈቃደኝነት ቀርበው ኩነቶቹን ካስመዘገቡ በኋላ ማስረጃ ለሚፈልጉ ግለሰቦች የምስክር ወረቀት እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተሳታፊዎች
ሀ. ማዘጋጃ ቤቶች
የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ካላቸው ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ የወሳኝ ኩነቶች ማስረጃን ከ193ዐዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በቁጥር 172/1946 ስለ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ቻርተር የወጣ የመንግስት ማስታወቂያ ነው፡፡ በቻርተሩ ምዕራፍ አንድ በቁጥር 3 “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለከተማው  አስተዳደር  የሚሆኑትን  ሕጎች  ለማዘጋጀትና ለማውጣት የሀገሩቷን ህጎች በከተማው ክልል ውስጥ በተሻለ ሁኔታ ለማስፈጸምና ስራ ላይ ለማዋል አስፈላጊ የሆኑትን የውስጥ ደንቦች ለማውጣት የህግ መብት ይኖረዋል የሚል ነው፡፡
ማዘጋጃ ቤቱ ለሚያከናውናቸው የምዝገባ ተግባራት ሕጋዊነት እየተወሰደ ያለው በ1952 በወጣው የፍትሐ- ብሔር ሕግ ውስጥ የተካተተውን ስለ ክብር መዝገብ ያሉትን አንቀፆች ሲሆን የጋብቻ ኩነት ምዝገባን በተመለከተ ደግሞ በ1992 ዓ.ም በወጣው የፌዴራል  የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ መሰረት ለመመዝገብ የተደራጀ መሆኑን ነው፡፡
የዓለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሠራር መርሆዎችን በተሟላ መንገድ በመከተል ባይሆንም ማዘጋጃ ቤቱ እና የክልል ከተማ ማዘጋጃ ቤቶች በግለሰቦች ፍላጐት እና ፍቃድ የሚቀርቡላቸውን የልደት፣ የጋብቻ፣ ያላገባ፣ የሞት፣ የፍቺ ጥያቄዎችን ተቀብለውና መርምረው ካጣሩ በኋላ ማስረጃ ይሰጣሉ፡፡ ከነዚህም ጋር የማስረጃዎች ግልባጭ የመስጠትና ከሌሎች አካላት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ማናቸውንም ከወሳኝ ኩነቶች ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን የማጣራት ተግባር ያከናውናሉ፡፡
ለ.የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ
በአዋጅ ቁጥር 3ዐ3/1964 ዓ.ም እና ትዕዛዝ ቁጥር 79/1964 ዓ.ም ጠቅላይ ስታትስቲክስ  ጽ/ቤት አንድ የመንግስት መ/ቤት ሆኖ ተቋቋመ፡፡ ጽ/ቤቱ በየጊዜው በየዘርፋ ከሚያጠናቸው በርካታ ጥናቶች ጋር በማቀናጀት የናሙና የቫይታል /የወሳኝ ኩነቶች/ ስታትስቲክስ ጥናት ለበርካታ አመታት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት እስከ 199ዐዎቹ መጀመሪያ ድረስ በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የናሙና ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ የቫይታል ስታትስቲክስ የጥናት ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡ ከ199ዐዎቹ መጀመሪያ በፊት ኤጀንሲው የተሻለ የቫይታል/ የወሳኝ ኩነቶች/ ስታትስቲክስ መረጃ ለማግኘት የሚያስችሉ የስታትስቲክስ የሙያ አጠናን ዘዴዎችን በመጠቀም የወሊድ፣ የሞት፣ ጋብቻና ፍቺን መጠን የመገመት ስራዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 442/1997 ዓ.ም በተሰጠው ስልጣን እና ከዓላማዎቹ አንዱ በሆነው በቆጠራ፣ በናሙና ጥናት፣ በማያቋርጥ ምዝገባና ከአስተዳደር መዛግብት የተሰበሰቡ የኢኮኖሚያዊ፣ የማህበራዊና የስነ-ህዝብ፣ የስታቲስቲክስ መረጃዎችን በተቀናጀ አሰራር ሰብስቦ፣ አቀናብሮና ተንትኖ ለተጠቃሚዎች የሚያሰራጭ የቫይታል ስታትስቲክስ ምዝገባ ጥናትና ምርምር መምሪያ እንዲቋቋም አድርጓል፡፡
ከ1990ቹ መጀመሪያ አንስቶ የአጠናን ስልቱን በመቀየር ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር እና ከተወሰኑ የክልል መስተዳድሮች (ትግራይ፣ አማራና የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል) ጋር በመቀናጀት በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ አግባባዊውን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አሰራር የተከተሉ የኩነቶች የሙከራ ጥናትለማካሄድ ችሏል፡፡
ሐ. የጤና ተቋማት
የጤና ተቋማት ከሚሰጡት የጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ በተቋማቱ ውስጥ የሚከሰቱትን የልደትና ሞት ክስተቶችን በተቋሙ ስለመከሰታቸው የህክምና የምስክር ወረቀት ይሰጣሉ፡፡ በጤና ተቋማቱ ውስጥ የስታትስቲክስ መረጃዎችን የሚያጠናቅሩ ሰራተኞች በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የክፍል ሃላፊዎች በማዕከል በተዘጋጁ ቅፆች ላይ በተቋማቱ የተከሰቱትን የልደትና የሞት ኩነቶችን አስመልክቶ የሚሞሉትን መረጃዎች ከሌሎች የተቋሙ መረጃዎች ጋር በማጠናቀር ለሚመለከተው የበላይአካል ያስተላልፋሉ፡፡
የጤና ተቋማት የሞት ኩነትን በተቋማቱ ስለመከሰቱ በሁለት መንገዶች ያረጋግጣሉ፡፡ የሞት ኩነቱ በአንድ በኩል ወደ ጤና ተቋም ለህክምና በመጣ ሰው ላይ የተከሰተ ከሆነ ሕክምናውን ሲያከናውን የነበረው ሐኪም የሞት የሕክምና የምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ለጠያቂው አካል ይሠጣል፡፡ የሞት ኩነቱ የተከሰተው ከተቋሙ ውጪ ሆኖ ግለሰቡ የሞተበትን ምክንያት ለማወቅ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ዘመድ ወይም ወዳጅ ሲጠይቅ የአስክሬን ምርመራ አድርጎ በሕግ ተቀባይነት ያለውን የምስክር ወረቀት ይሰጣል፡፡
ሀገራችን በጤና ተቋማት ውስጥ የሚከሰቱ የልደትም ሆነ የሞት ክስተቶች በጣም ጥቂቶች ከመሆናቸው በላይ በሁሉም የጤና ተቋማት የልደት ወይም የሞት መከሰትን የሚያረጋግጥ የህክምና የምስክር ወረቀት እንዲሰጡ የሚያደርግና አፈፃፀሙን የሚከታተል ወጥ አሠራር በጤና ተቋማት የሚደረገው የልደትና ሞት መከሰት ማስረጃ አሠጣጥ አግባባዊ የወሣኝ ኩነቶች ምዝገባ አሠራርን በመደገፍም ሆነ ግብአት የሚሆን መረጃ በማዘጋጀት በኩል  ክፍተት የመሙላት ስራ ይጠበቃል፡፡
መ. የሃይማኖት ተቋማት
ከላይ በተጠቀሱት የመንግስትና የኃይማኖት ተቋማት ሀይማኖታዊ አሰራርን ተከትለው ለበርካታ አመታት በፊት ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ሠ. ፕላን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህጻናት ፖሊሲ
በሀገሪቱ አግባባዊ የምዝገባ ስርዓት እንዲቋቋም ጥረት ካደረጉ ተቋማት መካከል ፕላን ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህጻናት ፖሊሲ መድረክ የተባሉ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነና በኢትዮጵያ የልደት ምዝገባ የአሰራር ልምድና ዕውቀት ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ ጥናት በአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ላይ አድርገዋል፡፡ የዚህ ጥናት ሪፖርት በስፋት እንዲሰራጭ በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተከናውኗል፡፡
ረ. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ላይ ሀገር አቀፍ ጉባኤ በማካሄድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ተከናውኗል፡፡
ሸ. የፍትህና ህግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት
የፍትህና ህግ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት በ1992 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ህግ ውስጥ የተመለከቱ የክብር መዝገብ አንቀጾችን መሰረት በማድረግ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ስርዓትና ተቋማዊ አደረጃጁትን ማቋቋሚያ ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት ለመንግስት ለማቅረብ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡
ቀ. የኢትዮጵያ ስነ-ሕዝብ ፖሊሲ
የኢትዮጵያ ስነ-ሕዝብ ፖሊሲ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አስገዳጅ በሆነ የምዝገባ ህግ መደገፍ እንደሚገባውና ምዝገባን የሚያካሂድ ተቋም የማደራጀት ኃላፊነትን ለስነ-ሕዝብ ጽ/ቤት ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪ በፖሊሲው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን / ኤጀንሲ/ የወሳኝ ኩነትን ምዝገባ ሥርዓትን ለማቋቋም እገዛ እንደሚያደርግ ተቀምጧል፡፡
ከላይ በተገለጸው መሰረት መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ እንዲሁም የሃይማኖት ድርጅቶች ከተደረጉ ጥረቶች በተጨማሪ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማቀድ፣ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ዜጐች ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግና በፍትሕ አስተዳደር ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራር እንዲኖር በማድረግ በሀገሪቱ ዘመናዊና የመልካም የሕዝብ አስተዳደር እንዲሰፍን ለማስቻል የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን በመገንዘብ ወደ ተጨባጭ አግባባዊ የወሳኝ ኩነት ምዘገባ ስርዓት ለመሸጋገር የማዕዘን ድንጋይ የሆነውን የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሄራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 76ዐ/2ዐዐ4 ዓ.ም እንዲሁም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 278/2ዐዐ5 ዓም አውጥቷል፡፡
ከዛም በተጨማሪ የወሳኝ ኩነት ምዝጋባ ስራ በሃገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ቀበሌዎች ምዝገባ ከተጀመረ በኋላ በምዝገባ አፈፃፀሙ ላይ የታዩትን የህግ ክፍተቶች በማስተካከል አዋጅ 1049/2009 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ በማድረግ ሁለቱ ተቋማት እስከሚዋሃዱ ድረስ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡
የኢምግሬሽን ታሪክ ስንመለከት፡- ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የኢሚግሬሽን አገልግሎት አሰጣጥ በዘመናዊ አስተዳደር ባይጀምርም የውጭ ሃገር ዜጐች ከንጉሰ ነገስቱ በሚሰጥ ፈቃድ ወደ አገር መግባትና በሀገር ውስጥ መቆየት ፈቃድ ይሰጥ ነበር፡፡ ጉብኝታቸውን ከጨረሱ በኃላ በመጡበት እንዲመለሱ ይደረግ እንደነበረ ታሪክ ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ምክንያት ማለት ለህክምና፣ ለወታደራዊ አማካሪዎች እና ለሚሽንሪዎች በተፃፈ ደብዳቤ ፈቃድ ይሰጥ ነበር፡፡
ከ1879 ዓ.ም ጀምሮ አሰራሩን በመጠኑ ተቋማዊ ለማድረግ የተጀመረበትና ወደ ሀገር የሚገቡ የውጭ ሃገር ዜጐች ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ንጉሰ ነገስቱ (ከአፄ ዮሃንስ አራተኛ) በሚፈቀደው ፈቃድ መሠረት የንጉሱ ፊርማ ያረፈበት የፈቃድ ደብዳቤ ለአገር ገዥዎች (አስተዳዳሪዎች) እንዲያውቁት ተደርጐ የውጭ ዜጋው ከመግቢያ በር ጀምሮ ንጉሱ ያሉበት ከተማ ድረስ እንዲመጡ ሲደረግ የውጭ ሃገር ዜጋው በጉዞው ወቅት በየደረሰበት ሥፍራ ሁሉ ያሉ አስተዳዳሪዎች እያስተናገዱት ደህንነቱን ጠብቀው በቅብብሎሽ የሚያደርሱት ሲሆን በዚህ ጉዞ ወቅት የውጭ ዜጋውን እያስተናገደ፣ ማደሪያ እየሰጠ እና እየመገበ በበቅሎ አጓጉዞ የማድረስ ሃላፊነት የአካባቢው አስተዳደሮች ላይ የተጣለና የውጭ ዜጋውን በመንገዱ ላይ አደጋ እንዳይደርስበት እና ከአውሬ እየጠበቀ የማድረስ ግዴታ ተጥሎበት ነበር፡፡
የውጭ ሃገር ዜጋውም ከላይ በተጠቀሰው መልኩ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ የመጣበትን ሥራ ጨርሶ ሲወጣ በተመሳሳይ መልኩ ከሀገር እንዲወጣ ከንጉሰ ነገስቱ የመውጫ ደብዳቤ ተሰጥቶት በገባበት በር በኩል እንዲወጣ ይደረግ ነበረ፡፡ ሂደቱ እንደ ቀጠለ ሆኖ ከአፄ ዮሃንስ አራተኛ በኃላ የመጡት አፄ ሚኒሊክበ1900 ዓ.ም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአዋጅ ሲቋቋሙ ይኸው የኢሚግሬሽን ቢሮ አደረጃጀቱ በአገር ግዛት ሚኒስቴር ሥር የፀጥታ ዴሬክሲዩን ተብሎ በሚጠራው የሥራ ክፍል ውስጥ አንድ ክፍል ሆኖ የተዋቀረ ሲሆን ይኸውም አወቃቀር ወይም አደረጃጀት በዘመነ ኃይለስላሴ ጊዜም በተመሳሳይ መልኩ እንዲቀጥል ተደርጎ በ1934 ዓ.ም የኢሚግሬሽን አዋጅ የወጣ ቢሆንም አደረጃጀቱ ሳይቀየር በክፍል ደረጃ የነበረና የሰው ሃይሉ አደረጃጀቱም በጣም አነስተኛ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ፡፡
ከ1966 ዓ.ም የንጉሳዊ ስርዓቱ በኋላ ደርግ ስልጣኑን እንደያዘ በህዝብ  ደህንነት ጥበቃ መሥሪያ ቤት ስር “የይለፍ ክፍል” ተብሎ እስከ 1972 ዓ.ም ድረስ እየሰራ እያለ ከ1972 ዓ.ም መጨረሻ እሰከ 1980 ዓ.ም ባለው ጊዜያት ወደ መምሪያ ከፍ በማድረግ ስያሜውንም የይለፍና ኰንስለር መምሪያ በማለት እንዲዋቀር ተደርጐ ሲሰራ ከቆየ በኋላ በ198ዐ ዓ.ም አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተብሎ በሚኒስቴር ደረጃ ሲቋቋም ቀደም ተብሎ ሲጠራበት የነበረው ስም ተቀይሮ የኢሚግሬሽንና የስደተኞች ጉዳይ ዋና መምሪያ ተብሎ በዋና መምሪያ ደረጃ እንዲቋቋም ተደርጐ ነበር፡፡
ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ዘመኑ ከደረሰበት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተጣጣመና በየጊዜው እየጎለበተ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እንዲሰራ በማድረግ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት አሰራሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና አለም የደረሰበት ሁኔታ ጋር አሰራሩን እያዘመነ ወቅቱ የሚጠይቀውን አደረጃጀት በመፍጠር ዘመናዊ የኢሚግሬሽን አሰራር በመከተል ቀደም ሲል በማንዋል ፖስፓርት ይሰጥ የነበረውን በማስቀረት ኤሌክትሮኒካል ፖስፓርት መስጠት እንዲጀመር ማድረግ ተችሏል፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችውን  ተግባር ለማከናወን በርካታ ዘመናዊ መሳሪያዎች መጠቀም ተጀምሯል፡፡
በ2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጽያ ከተጀመረው የሪፎርም ለውጥ ስራዎች ውስጥ አንዱ የኢሚግሬሽን አገልግሎት በመሆኑ አገልግሎቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶት ከወሳኝ ኩነት ጋር በመዋሀድ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ጉነት ኤጀንሲ በሚል ስያሜ እንደ አዲስ እንዲቋቋም በማድረግ ቀጣነት ባለው ሪፎርም ስራዎች አገልግሎቱን በአግባቡ መስጠት የሚያስችለውን አቅም እየገነባ እየሄደ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱን በአግባቡ መስጠት የሚያስችለውን አቅም እየገነባ እየሄደ ይገኛል፡፡